← Exodus (4/40) → |
1. | ሙሴም መለሰ። እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም። እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ። |
2. | እግዚአብሔርም። ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም። በትር ናት አለ። |
3. | ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ። |
5. | እግዚአብሔርም ሙሴን። የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ እግዚአብሔር እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ እጅህን ዘርግተህ ጅራትዋን ያዝ አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዛት በእጁም ውስጥ በትር ሆነች። |
6. | እግዚአብሔርም ደግሞ። እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። |
7. | እርሱም። እጅህን ወደ ብብትህ መልስ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች። |
8. | ደግሞም አለው። እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ። |
9. | እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፥ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል። |
10. | ሙሴም እግዚአብሔርን። ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። |
11. | እግዚአብሔርም። የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? |
12. | እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው። |
13. | እርሱም። ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። |
14. | የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ። ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። |
15. | አንተም ትናገረዋለህ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። |
16. | እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ። |
17. | ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። |
18. | ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ። እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ አለው። ዮቶርም ሙሴን። በሰላም ሂድ አለው። |
19. | እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም። ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ አለው። |
20. | ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። |
21. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። |
22. | ፈርዖንንም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። |
23. | እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ ትለዋለህ። |
24. | እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። |
25. | ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፥ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው። አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች። |
26. | ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ። ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች። |
27. | እግዚአብሔርም አሮንን። ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። |
28. | ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ተናገረው። |
29. | ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። |
30. | አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። |
31. | ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጐነበሱ ሰገዱም። |
← Exodus (4/40) → |