← Exodus (39/40) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ። |
2. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ። |
3. | ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ። |
4. | ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት። |
5. | በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ። |
6. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። |
7. | ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ አደረጋቸው። |
8. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገው። |
9. | አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱን ኪስም ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። |
10. | ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤ |
11. | በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤ |
12. | በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤ |
13. | በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ። |
14. | የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ አሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ አሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። |
15. | ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ። |
16. | ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አደረጉ። |
17. | ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ። |
18. | የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ። |
19. | ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው። |
20. | ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው። |
21. | የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ጋር ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት። |
22. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የኤፉዱን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አደረገው። |
23. | በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ። |
24. | በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ። |
25. | ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፥ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። |
26. | በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኵራንና ሮማንን ለማገልገል አደረጉ። |
27. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ሸሚዞችን፥ |
28. | ከጥሩ በፍታም መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የእግር ሱሪዎችን፥ |
29. | ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን አደረጉ። |
30. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት። |
31. | በመጠምጠሚያውም ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት። |
32. | እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። |
33. | ማደሪያውንም፥ ድንኳኑንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ |
34. | ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፤ |
35. | የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤ |
36. | ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ |
37. | ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤ |
38. | የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤ |
39. | የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ |
40. | የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው ማገልገያ የሚሆኑን ዕቃዎች ሁሉ፤ |
41. | በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ። |
42. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ። |
43. | ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው። |
← Exodus (39/40) → |