| ← Exodus (37/40) → |
| 1. | ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። |
| 2. | በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። |
| 3. | አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። |
| 4. | መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። |
| 5. | ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ። |
| 6. | ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ። |
| 7. | ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው። |
| 8. | ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው። |
| 9. | ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ። |
| 10. | ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ። |
| 11. | በጥሩም ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። |
| 12. | በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። |
| 13. | አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። |
| 14. | ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ። |
| 15. | ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። |
| 16. | ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን ጽዋዎቹንም መቅጃዎቹንም፥ ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው። |
| 17. | መቅረዙንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጕብጕቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ። |
| 18. | በስተ ጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ወጡ። |
| 19. | በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። |
| 20. | በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። |
| 21. | ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ። |
| 22. | ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። |
| 23. | ሰባቱንም መብራቶች መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። |
| 24. | መቅረዙንም ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ። |
| 25. | የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ። |
| 26. | ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። |
| 27. | ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ነበሩ። |
| 28. | መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፥ በወርቅም ለበጣቸው። |
| 29. | የተቀደሰውንም የቅብዓቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ። |
| ← Exodus (37/40) → |