| ← Exodus (35/40) → |
| 1. | ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ታደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ይህ ነው፤ |
| 2. | ስድስት ቀን ሥራ ይደረጋል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የዕረፍት ሰንበት የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል። |
| 3. | በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ። |
| 4. | ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ |
| 5. | ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቍርባን ያምጣ፤ ወርቅና ብርም ናስም፤ |
| 6. | ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤ |
| 7. | ቀይም የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣም ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፤ |
| 8. | ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፤ |
| 9. | መረግድ ለኤፉዱና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። |
| 10. | በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ። |
| 11. | ማደሪያውን፥ ድንኳኑንም መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ |
| 12. | ታቦቱን መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም በእርሱም ፊት የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ |
| 13. | ገበታውን መሎጊያዎቹንም ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ |
| 14. | መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን ዕቃውንም፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ |
| 15. | የዕጣኑን መሠዊያም መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ |
| 16. | ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፤ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ |
| 17. | የአደባባዩን መጋረጆች ምሰሶቹንም እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ |
| 18. | የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች አውታሮቻቸውንም፤ |
| 19. | በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች። |
| 20. | የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ። |
| 21. | ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። |
| 22. | ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ። |
| 23. | ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበትም፥ የአቆስጣ ቁርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። |
| 24. | ስእለት የተሳለ ሁሉ የብርንም የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የግራርም እንጨት ያለው ሁሉ ለማገልገያ ሥራ አመጣ። |
| 25. | በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። |
| 26. | ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። |
| 27. | አለቆችም መረግድን፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ |
| 28. | ለመብራትም ለቅብዓት ዘይትም ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። |
| 29. | ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ። |
| 30. | ሙሴም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። እዩ፥ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። |
| 31. | በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት፤ |
| 32. | የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ፥ |
| 33. | በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። |
| 34. | እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው። |
| 35. | በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ በቀይም ግምጃ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ። |
| ← Exodus (35/40) → |