← Exodus (34/40) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። |
2. | ነገም የተዘጋጀህ ሁን፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። |
3. | ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ። |
4. | ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፥ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ወሰደ፥ |
5. | እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። |
6. | እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ። እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ |
7. | እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። |
8. | ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ። |
9. | አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና ጌታዬ በመካከላችን ይሂድ፤ ጠማማነታችንንና ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ ለርስትህም ተቀበለን አለ። |
10. | እርሱም አለው። እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ተአምራት በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤ እኔም በአንተ ዘንድ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና አንተ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። |
11. | በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም በፊትህ አወጣለሁ። |
12. | በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትሄድባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ |
13. | ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውንም ትሰብራላችሁ፥ የማምለኪያ ዓፀዶቻቸውንም ትቈርጣላችሁ፤ |
14. | ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። |
15. | በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ |
16. | ሴት ልጆቻቸውንም ከወንድ ልጆችህ ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። |
17. | ቀልጠው የተሠሩትን የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ። |
18. | የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በአቢብ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ። |
19. | ማኅፀንንም የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባት በኵር ሁሉ፥ በሬም ቢሆን በግም ቢሆን፥ የእኔ ነው። |
20. | የአህያውንም በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። |
21. | ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። |
22. | የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። |
23. | በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። |
24. | አሕዛብን ከፊትህ አወጣለሁ፥ አገርህንም አሰፋለሁ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። |
25. | የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። |
26. | የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ታገባለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅልም። v |
27. | እግዚአብሔርም ሙሴን። በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። |
28. | በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። |
29. | እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። |
30. | አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። |
31. | ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩን አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። |
32. | ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። |
33. | ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። |
34. | ሙሴም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገረ። |
35. | የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት ቁርበት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር። |
← Exodus (34/40) → |