← Exodus (30/40) → |
1. | የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው። |
2. | ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱም አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ። |
3. | ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። |
4. | ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት። በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ። |
5. | መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው። |
6. | በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ ይህንም አንተን በምገናኝበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ። |
7. | አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው። |
8. | ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል። |
9. | ሌላም ዕጣን፥ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቍርባን አታፈስስበትም። |
10. | አሮንም በአመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በአመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን ናት። |
11. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
12. | አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ። |
13. | አልፎ የሚቈጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል። |
14. | ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቈጠረ ሁሉ፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል። |
15. | ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ድሀውም አያጕድል። |
16. | የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን። |
17. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
18. | የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ። |
19. | አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል። |
20. | ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ፥ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል። |
21. | እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል። |
22. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
23. | አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ፤ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ |
24. | ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ። |
25. | በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል። |
26. | የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ |
27. | ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ |
28. | ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። |
29. | ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። |
30. | በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም። |
31. | አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር። ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሁንልኝ። |
32. | በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱም የተሰራ ሌላ ቅብዓት አታድርጉ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን። |
33. | እንደ እርሱ ያለውን የሚያደርግ ሰው፥ በሌላም ሰው ላይ የሚያፈስሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። |
34. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም እጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ትክክል ይሁን። |
35. | በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፥ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው። |
36. | ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ። |
37. | እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን። |
38. | ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። |
← Exodus (30/40) → |