← Exodus (28/40) → |
1. | አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን አብዮድንም አልዓዛርንም ኢታምርንም፥ አቅርብ። |
2. | የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። |
3. | አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። |
4. | የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ ኤፉድም ቀሚስም ዝንጕርጕር ሸሚዝም መጠምጠሚያም መታጠቂያም፤ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። |
5. | ወርቅንም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። |
6. | ኤፉዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ። |
7. | ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን። |
8. | በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን። |
9. | ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ |
10. | እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ። |
11. | በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅም ፈርጥ አድርግ። |
12. | የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቍዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል። |
14. | የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጐነጐነም ገመድ አድርግ፤ የተጐነጐኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል። |
15. | ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም ሥራው። |
16. | ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል። |
17. | በአራት ተራ የሆነ የዕንቍ ፈርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤ |
18. | በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤ |
19. | በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤ |
20. | በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ። |
21. | የዕንቈቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ። |
22. | ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው። |
23. | ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው። |
24. | የተጐነጐኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ። |
25. | የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ። |
26. | ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። |
27. | ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። |
28. | የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል። |
29. | አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። |
30. | በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። |
31. | የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው። |
32. | ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት። |
33. | በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኵራዎች አድርግ፤ |
34. | የወርቅ ሻኵራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኵራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። |
35. | በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። |
36. | ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ። |
37. | በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ። |
38. | በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን። |
39. | ሸሚዙንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራር መታጠቂያም ትሠራለህ። |
40. | ለአሮንም ልጆች ሸሚዞችን መታጠቂያዎችንም ቆቦችንም ለክብርና ለጌጥ ታደርግላቸዋለህ። |
41. | ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ። |
42. | ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ |
43. | ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው እንዳይሞቱም፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል። |
← Exodus (28/40) → |