| ← Exodus (27/40) → |
| 1. | ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። |
| 2. | በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው። |
| 3. | አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። |
| 4. | እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። |
| 5. | መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ በመሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው። |
| 6. | ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው። |
| 7. | መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ። |
| 8. | ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት። |
| 9. | የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤ |
| 10. | ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት፤ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ። |
| 11. | እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ፤ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ። |
| 12. | በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት። |
| 13. | በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን። |
| 14. | በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። |
| 15. | በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። |
| 16. | ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፤ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ። |
| 17. | በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው። |
| 18. | የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን፤ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ። |
| 19. | ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ። |
| 20. | አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። |
| 21. | በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን። |
| ← Exodus (27/40) → |