| ← Exodus (26/40) → |
| 1. | ደግሞም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ የተሠሩ አሥር መጋረጆች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። |
| 2. | የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን። |
| 3. | አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። |
| 4. | ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። |
| 5. | አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ። |
| 6. | አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ ማደሪያውንም አንድ እንዲሆን መጋረጆችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። |
| 7. | ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጕር አድርግ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች ታደርጋለህ። |
| 8. | እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ይሁን። |
| 9. | አምስቱ መጋረጆች አንድ ሆነው ይጋጠሙ፥ ስድስቱም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። |
| 10. | ከተጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንድኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። |
| 11. | አምሳም የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፥ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን አጋጥመው። |
| 12. | ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። |
| 13. | ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። |
| 14. | ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አድርግ። |
| 15. | ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቆች ከግራር እንጨት አድርግ። |
| 16. | የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። |
| 17. | ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። |
| 18. | ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አድርግ። |
| 19. | ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። |
| 20. | ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች፥ |
| 21. | ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። |
| 22. | ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቆችን አድርግ። |
| 23. | ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆችን አድርግ። |
| 24. | ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። |
| 25. | ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። |
| 26. | ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ |
| 27. | በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። |
| 28. | መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። |
| 29. | ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። |
| 30. | ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም። |
| 31. | መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። |
| 32. | በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። |
| 33. | መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። |
| 34. | በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። |
| 35. | ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። |
| 36. | ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። |
| 37. | ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው። |
| ← Exodus (26/40) → |