← Exodus (24/40) → |
1. | ሙሴንም። አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ |
2. | ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው። |
3. | ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። |
4. | ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። |
5. | የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ። |
6. | ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። |
7. | የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። |
8. | ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ። |
9. | ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ |
10. | የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። |
11. | እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም። |
12. | እግዚአብሔርም ሙሴን። ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው። |
13. | ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። |
14. | ሽማግሌዎችንም። ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው። |
15. | ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። |
16. | የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። |
17. | በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። |
18. | ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ። |
← Exodus (24/40) → |