Exodus (23/40)  

1. ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ።
2. ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር።
3. በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ።
4. የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት።
5. የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አንሣው።
6. በሚምዋገትበት ጊዜ የድሀህን ፍርድ አታጥምም።
7. ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጻድቅን አትግደል።
8. ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።
9. በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና።
10. ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ፍሬዋንም አግባ፤
11. በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህም ድሆች ይበሉታል፤ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። እንዲሁም በወይንህና በወይራህ አድርግ።
12. ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ ያርፉ ዘንድ ለባሪያህም ልጅ ለመጻተኛውም ዕረፍት ይሆን ዘንድ በሰባተኛው ቀን ዕረፍ።
13. ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፋችሁም አይሰማ።
14. በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ታደርግልኛለህ።
15. የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ።
16. በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ።
17. በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ።
18. የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር።
19. የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣ። ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል።
20. በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።
21. በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።
22. አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ።
23. መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ።
24. ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው።
25. አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ።
26. በምድርህም መካን ወይም የምትጨነግፍ አትሆንም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ።
27. መፈራቴንም በፊትህ እሰድዳለሁ፥ የምትሄድበትንም ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ።
28. በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ።
29. ምድር ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ከፊታችሁ አላባርራቸውም።
30. ነገር ግን እስክትበዛ ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ።
31. ድንበርህንም ከኤርትራ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳም እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድር የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፤ ከፊትህም ታባርራቸዋለሁ።
32. ከእነርሱና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ።
33. አማልክቶቻቸውንም ብታመልክ ወጥመድ ይሆኑብሃልና እኔን እንድትበድል እንዳያደርጉህ በአገርህ አይቀመጡ።

  Exodus (23/40)