← Exodus (21/40) → |
1. | በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው። |
2. | ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ። |
3. | ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ። |
4. | ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ፥ እርሱም ብቻውን ይውጣ። |
5. | ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥ |
6. | ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን። |
7. | ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ። |
8. | ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። |
9. | ለልጁም ብድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት። |
10. | ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት። |
11. | ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ። |
12. | ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። |
13. | ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ። |
14. | ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውን በተንኰል ቢገድለው፥ እንዲሞት ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው። |
15. | አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። |
16. | ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። |
17. | አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል። |
18. | ሁለት ሰዎችም ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን ታምሞ በአልጋው ላይ ቢተኛ፥ |
19. | ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይከፍለው ዘንድ፥ ያስፈውሰውም ዘንድ ግዴታ አለበት። |
20. | ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ። |
21. | የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ። |
22. | ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል። |
23. | ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥ |
24. | ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ |
25. | እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል። |
26. | ሰውም የባሪያውን ወይም የባሪይይቱን ዓይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ አርነት ያውጣው። |
27. | የባሪያውን ወይም የባሪያይቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ አርነት ያውጣው። |
28. | በሬም ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው። |
29. | በሬው ግን አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባይጠብቀውም፥ ወንድንም ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል። |
30. | ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ዎጆ የጫኑበትን ያህል ይስጥ። |
31. | ደግሞ ወንድን ልጅ ቢወጋ ሴትንም ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት። |
32. | በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር። |
33. | ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅበት፥ |
34. | የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን። |
35. | የሰው በሬ የሌላውን በሬ እስኪሞት ድረስ ቢወጋ፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ። |
36. | በሬውም አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው። |
← Exodus (21/40) → |