← Exodus (19/40) → |
1. | በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። |
2. | ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። |
3. | ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር። |
4. | በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። |
5. | አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ |
6. | እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው። |
7. | ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። |
8. | ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ። |
9. | እግዚአብሔርም ሙሴን። ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘላለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ። |
10. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ |
11. | በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ። |
12. | ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው። ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤ |
13. | የማንም እጅ አይንካ፤ ነገር ግን የሚነካው ሁሉ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን አይድንም በላቸው። ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ። |
14. | ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ። |
15. | ሕዝቡንም። ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴቶቻችሁ አትቅረቡ አለ። |
16. | እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። |
17. | ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ። |
18. | እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር። |
19. | የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። |
20. | እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ። |
21. | እግዚአብሔርም ሙሴን። ውረድ፥ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤ |
22. | ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ አለው። |
23. | ሙሴም እግዚአብሔርን። አንተ። በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም አለው። |
24. | እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይተላለፉ አለው። |
25. | ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ይህንንም ነገራቸው። |
← Exodus (19/40) → |