| ← Exodus (17/40) → |
| 1. | የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፥ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም። |
| 2. | ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም። ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው። |
| 3. | ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ። እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ሲሉ በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። |
| 4. | ሙሴም። ሊወግሩኝ ቀርበዋልና በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። |
| 5. | እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። |
| 6. | እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። |
| 7. | ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር። እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው። |
| 8. | አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር በራፊድም ተዋጋ። |
| 9. | ሙሴም ኢያሱን። ጕልማሶችን ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው። |
| 10. | ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። |
| 11. | እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። |
| 12. | የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ። |
| 13. | ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። |
| 14. | እግዚአብሔርም ሙሴን። የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ ተናገር አለው። |
| 15. | ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም ይህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፤ |
| 16. | እርሱም። እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ። |
| ← Exodus (17/40) → |