← Exodus (15/40) → |
1. | በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። |
2. | ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። |
3. | እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥ |
4. | የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። |
5. | ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። |
6. | አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። |
7. | በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። |
8. | በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። |
9. | ጠላትም። አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። |
10. | ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። |
11. | አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? |
12. | ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። |
13. | በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። |
14. | አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። |
15. | የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። |
16. | አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ። |
17. | አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። |
18. | እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል። |
19. | የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ። |
20. | የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። |
21. | ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። |
22. | ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። |
23. | ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። |
24. | ሕዝቡም። ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። |
25. | ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ |
26. | እርሱም። አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ። |
27. | እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ። |
← Exodus (15/40) → |