| ← Exodus (14/40) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። |
| 3. | ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች። በምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል። |
| 4. | እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። |
| 5. | ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና። እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል? አሉ። |
| 6. | ሰረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ |
| 7. | ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ። |
| 8. | እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። |
| 9. | ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው። |
| 10. | ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። |
| 11. | ሙሴንም። በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? |
| 12. | በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት። |
| 13. | ሙሴም ለሕዝቡ። አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። |
| 14. | እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። |
| 15. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። |
| 16. | አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። |
| 17. | እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። |
| 18. | ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
| 19. | በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ |
| 20. | በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። |
| 21. | ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ። |
| 22. | የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። |
| 23. | ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። |
| 24. | ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። |
| 25. | የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም። እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ። |
| 26. | እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኃውም በግብፃውያን በሰረገሎቻቸውም በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ አለው። |
| 27. | ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። |
| 28. | ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። |
| 29. | የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው። |
| 30. | እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ። |
| 31. | እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፥ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፥ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ። |
| ← Exodus (14/40) → |