| ← Exodus (12/40) → |
| 1. | እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። |
| 2. | ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። |
| 3. | ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። |
| 4. | የቤቱ ሰዎች ቍጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። |
| 5. | የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። |
| 6. | በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። |
| 7. | ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት። |
| 8. | በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል። |
| 9. | ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። |
| 10. | ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት። |
| 11. | ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። |
| 12. | እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 13. | ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። |
| 14. | ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ። |
| 15. | ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። |
| 16. | በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላው በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፥ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ። |
| 17. | በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። |
| 18. | በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። |
| 19. | ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ። |
| 20. | እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ። |
| 21. | ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው። በየቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፥ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት። |
| 22. | ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ። |
| 23. | እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም። |
| 24. | ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ። |
| 25. | እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት። |
| 26. | እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ። ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው? |
| 27. | ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ። በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ። |
| 28. | ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። |
| 29. | እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ። |
| 30. | ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ። |
| 31. | ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ። እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ |
| 32. | እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ አለ። |
| 33. | ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኵሉአቸው ነበር። ሁላችን እንሞታለን ብለዋልና። |
| 34. | ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት። |
| 35. | የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። |
| 36. | እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ። |
| 37. | የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ። |
| 38. | ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። |
| 39. | ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ እንጎቻ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኰሉአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር። |
| 40. | የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድር የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። |
| 41. | እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ። |
| 42. | ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት። |
| 43. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አለ። ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ። |
| 44. | በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ። |
| 45. | መጻተኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ። |
| 46. | በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንትም አትስበሩበት። |
| 47. | የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት። |
| 48. | እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። |
| 49. | ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል። |
| 50. | የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። |
| 51. | በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ። |
| ← Exodus (12/40) → |