Exodus (1/40) → |
1. | ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ። |
2. | ሮቤል፥ |
3. | ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ |
4. | ብንያም፥ ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር። |
5. | ከያቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ። |
6. | ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ። |
7. | የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ አጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። |
8. | በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ። |
9. | እርሱም ሕዝቡን። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ |
10. | እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ። |
11. | በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ። |
12. | ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር። |
13. | ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው። |
14. | በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር። |
15. | የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ። |
16. | እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር። |
17. | አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው። |
18. | የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው። |
19. | አዋላጆቹም ፈርዖንን። የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት። |
20. | እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ጸና። |
21. | እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው። |
22. | ፈርዖንም። የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። |
Exodus (1/40) → |