| ← Esther (6/10) → | 
| 1. | በዚያም ሌሊት እንቅልፍ ከንጉሡ ሸሸ፤ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ በንጉሡም ፊት ተነበበ። | 
| 2. | ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ እጃቸውን በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ እንደ ፈለጉ፥ መርዶክዮስ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ። | 
| 3. | ንጉሡም። ስለዚህ ነገር ለመርዶክዮስ ምን ክብርና በጎነት ተደረገለት? አለ። ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች። ምንም አልተደረገለትም አሉት። | 
| 4. | ንጉሡም። በአዳራሹ ማን አለ? አለ። ሐማም ባዘጋጀው ግንድ ላይ መርዶክዮስን ለማሰቀል ለንጉሡ ይናገር ዘንድ ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ውጭው አዳራሽ ገብቶ ነበር። | 
| 5. | የንጉሡም ብላቴኖች። እነሆ ሐማ በአዳራሹ ቆሞአል አሉት። ንጉሡም። ይግባ አለ። | 
| 6. | ሐማም ገባ፤ ንጉሡም። ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለታል? አለው። ሐማም በልቡ። ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል? አለ። | 
| 7. | ሐማም ንጉሡን እንዲህ አለው። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ፤ | 
| 8. | ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የተቀመጠበት ፈረስ ይምጣለት፥ የንጉሡም ዘውድ በራሱ ላይ ይደረግ፤ | 
| 9. | ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት፤ ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር። | 
| 10. | ንጉሡም ሐማን። ፍጠን፥ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው አይሁዳዊ ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፤ ከተናገርኸውም ሁሉ ምንም አይቅር አለው። | 
| 11. | ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፥ መርዶክዮስንም አለበሰው፥ በፈረሱም ላይ አስቀመጠው፥ በከተማይቱም አደባባይ በፊቱ አሳለፈው። በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብሎ አዋጅ ነገረ። | 
| 12. | መርዶክዮስም ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን አዝኖና ራሱን ተከናንቦ ቸኵሎ ወደ ቤቱ ሄደ። | 
| 13. | ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ያገኘውን ሁሉ አጫወታቸው። ጥበበኞቹና ሚስቱ ዞሳራም። በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ከአይሁድ ወገን የሆነ እንደ ሆነ በፊቱ ፈጽሞ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም አሉት። | 
| 14. | እነርሱም ሲናገሩት ሳሉ እነሆ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፥ አስቴርም ወዳዘጋጀችው ግብዣ ይመጣ ዘንድ ሐማን አስቸኰሉት። | 
| ← Esther (6/10) → |