← Ecclesiastes (6/12) → |
1. | ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው። |
2. | እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። |
3. | ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነፍሱም መልካምን ባትጠግብ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ። ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። |
4. | በከንቱ መጥቶአል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፤ |
5. | ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፤ ለዚህም ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። |
6. | ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? |
7. | የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። |
8. | ከሰነፍ ይልቅ ለጥበበኛ ጥቅም ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድ ለሚያውቅ ለድሀ ጥቅሙ ምንድር ነው? |
9. | በዓይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። |
10. | የሆነው ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፤ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም። |
11. | ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? |
12. | ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል? |
← Ecclesiastes (6/12) → |