← Ecclesiastes (5/12) → |
1. | ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። |
2. | እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። |
3. | ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፤ እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። |
4. | ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው። |
5. | ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። |
6. | ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፥ በመልአክም ፊት። ስሕተት ነበረ አትበል፤ እግዚአብሔር በቃልህ ይቈጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ያጠፋ ዘንድ ስለምን ትሻለህ? |
7. | ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ፥ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ። |
8. | ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ። |
9. | በጠቅላላው ግን የአገሩ ጥቅም እርሻን የሚወድድ ንጉሥ ቢኖር ነው። |
10. | ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። |
11. | ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? |
12. | እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል። |
13. | ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። |
14. | ያችም ባለጠግነት በክፉ ነገር ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። |
15. | ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም። |
16. | ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፤ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድር ነው? |
17. | ዘመኑን ሁሉ በጨለማ በኀዘን በብስጭት በደዌና በቍጣ ነው። |
18. | እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። |
19. | እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። |
20. | እግዚአብሔር በልቡ ደስታን ስለ ሰጠው እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግ አያስብም። |
← Ecclesiastes (5/12) → |