| ← Ecclesiastes (3/12) → |
| 1. | ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። |
| 2. | ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ |
| 3. | ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ |
| 4. | ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ |
| 5. | ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ |
| 6. | ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ |
| 7. | ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ |
| 8. | ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። |
| 9. | ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው? |
| 10. | እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። |
| 11. | ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። |
| 12. | ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። |
| 13. | ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። |
| 14. | እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። |
| 15. | አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል። |
| 16. | ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ኃጢአት፥ በጽድቅም ስፍራ ኃጢአት እንዳለ አየሁ። |
| 17. | እኔም በልቤ። በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ። |
| 18. | እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች። እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ። |
| 19. | የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። |
| 20. | ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። |
| 21. | የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? |
| 22. | ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው? |
| ← Ecclesiastes (3/12) → |