| ← Deuteronomy (34/34) |
| 1. | ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም እስከዳን ድረስ ያለውን የገለዓድን ምድር፥ |
| 2. | የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴንም ምድር፥ እስከ ምዕራብም ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፥ ደቡብንም፥ |
| 3. | እስከ ዞዓር ድረስ ያለውንም የዘንባባ ዛፎች ያሉባትን ከተማ የኢያሪኮን ሸለቆ ሜዳ አሳየው። |
| 4. | እግዚአብሔርም። ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም አለው። |
| 5. | የእግዚአብሔር ባሪያም ሙሴ እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። |
| 6. | በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም። |
| 7. | ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ፤ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጕልበቱም አልደነገዘም። |
| 8. | የእስራኤልም ልጆች በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን ለሙሴ አለቀሱለት፤ ለሙሴም ያለቀሱለት የልቅሶው ወራት ተፈጸመ። |
| 9. | ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |
| 10. | እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም፤ |
| 11. | በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከው ያለ፥ |
| 12. | በእስራኤል ሁሉ ፊት በጸናች እጅ ሁሉና በታላቅ ማስደንገጥ ሁሉ እንዳደረገው እንደ ሙሴ ያለ አልተነሣም። |
| ← Deuteronomy (34/34) |