Deuteronomy (3/34)  

1. ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን፥ የባሳን ንጉሥ ዐግም ሕዝቡም ሁሉ በኤድራይ ሊዋጉን ወጡ።
2. እግዚአብሔርም። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ።
3. አምላካችን እግዚአብሔርም ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዐግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም መታነው፤ አንድ ሰው እንኳ አምልጦ አልቀረለትም።
4. በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፤ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን።
5. በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ።
6. በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ አጠፋናቸው፤ ከተሞቹን ሁሉ ከወንዶችና ከሴቶች ከሕፃናቶችም ጋር አጠፋናቸው።
7. ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለእኛ በዘበዝን።
8. በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤
9. ሲዶናውያን አርሞንዔምን ሢርዮን ብለው ይጠሩታል፥ አሞራውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል።
10. በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን።
11. ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በነበረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ።
12. ይህችንም ምድር በዚያን ዘመን ወረስን፤ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ አገር እኩሌታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው።
13. ከገለዓድም የቀረውን የዐግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፤ ያችም ባሳን ሁሉ የራፋይም አገር ተብላ ተቈጠረች።
14. የምናሴ ልጅ ኢያዕር እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ የአርጎብን ምድር ሁሉ ወሰደ፤ ይህችንም የባሳንን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ በስሙ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራ።
15. ለማኪርም ገልዓድን ሰጠሁት።
16. ለሮቤል ነገድና ለጋድም ነገድ ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥
17. ከኪኔሬት እስከ ዓረባ ባሕር እርሱም የጨው ባሕር ድረስ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን ዓረባ ዮርዳኖስንም ዳሩንም ሰጠኋቸው።
18. በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ አርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ።
19. ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤
20. ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።
21. በዚያም ጊዜ ኢያሱን። አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዓይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል።
22. አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና አትፍራቸውም ብዬ አዘዝሁት።
23. በዚያም ዘመን እኔ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ለመንሁ።
24. ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለባሪያህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይና በምድርም እንደ ሥራህ እንደ ኃይልህም ይሠራ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው?
25. እኔ ልሻገር በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር ያንም መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ልይ።
26. እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ አልሰማኝምም፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይበቃሃል፤ በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ።
27. ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ፈስጋ ራስ ውጣ፤ ዓይንህንም ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም አንሥተህ በዓይንህ ተመልከት።
28. ኢያሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና ኢያሱን እዘዘው፥ አደፋፍረውም፥ አጽናውም።
29. በቤተፌጎርም ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን።

  Deuteronomy (3/34)