| ← Deuteronomy (27/34) → |
| 1. | ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ብለው ሕዝቡን አዘዙ። ዛሬ ያዘዝኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ። |
| 2. | አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ ታላላቅ ድንጋዮችን ለአንተ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው። |
| 3. | የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ትገባ ዘንድ በተሻገርህ ጊዜ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ጻፍባቸው። |
| 4. | ዮርዳኖስንም በተሻገርህ ጊዜ፥ ዛሬ እንዳዘዝሁህ፥ እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው። |
| 5. | በዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ መሠዊያውም ብረት ካልነካው ድንጋይ ይሁን። |
| 6. | ካልተጠረበም ድንጋይ የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ሥራ፤ ለአምላክም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት፤ |
| 7. | የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዋበት፥ በዚያም ብላ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። |
| 8. | የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ የተገለጠ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ። |
| 9. | ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል። |
| 10. | ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ። |
| 11. | ሙሴም በዚያን ቀን እንዲህ ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። |
| 12. | ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ እነዚህ፥ ስምዖንና ሌዊ ይሁዳና ይሳኮር ዮሴፍና ብንያም፥ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ። |
| 13. | ይረግሙም ዘንድ እነዚህ፥ ሮቤልና ጋድ አሴርና ዛብሎን ዳንና ንፍታሌም፥ በጌባል ተራራ ላይ ይቁሙ። |
| 14. | ሌዋውያንም ከፍ ባለች ድምፅ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገራሉ። |
| 15. | በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ። |
| 16. | አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 17. | የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 18. | ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 19. | በመጻተኛ በድሀ አደጉም በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 20. | ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ልብስ ገልጦአልና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 21. | ከማናቸይቱም እንስሳ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 22. | ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 23. | ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 24. | ባልንጀራውን በስውር የሚመታ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 25. | የንጹሑን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| 26. | የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። |
| ← Deuteronomy (27/34) → |