| ← Deuteronomy (26/34) → |
| 1. | አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር በገባህም ጊዜ፥ በወረስሃትም በኖርህባትም ጊዜ፥ |
| 2. | አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ፍሬ ሁሉ በኵራት ውሰድ በዕንቅብም አድርገው፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠውም ስፍራ ይዘህ ሂድ። |
| 3. | በዚያም ወራት ወደሚሆነው ካህን መጥተህ። እግዚአብሔር ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስታውቃለሁ በለው። |
| 4. | ካህኑም ዕንቅቡን ከእጅህ ወስዶ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠውያ ፊት ያኑረው። |
| 5. | በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር። አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበረ፤ በቍጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ የሆነ የበረታም ቍጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ። |
| 6. | ግብፃውያንም ክፉ ነገር አደረጉብን፥ አስጨነቁንም፥ በላያችንም ጽኑ ከባድ ሥራን ጫኑብን፤ |
| 7. | ወደ አባቶቻችንም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ድምፃችንን ሰማ፥ ጭንቀታችንንም ድካማችንንም ግፋችንንም አየ፤ |
| 8. | እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ድንጋጤ፥ በተአምራትም፥ በድንቅም ከግብፅ አወጣን፤ |
| 9. | ወደዚህም ስፍራ አገባን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን። |
| 10. | አሁንም እነሆ፥ አቤቱ፥ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን ፍሬ በኵራት አቅርቤአለሁ። አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ስገድ። |
| 11. | አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ። |
| 12. | አሥራት በምታወጣበት በሦስተኛው ዓመት የፍሬህን ሁሉ አሥራት አውጥተህ በፈጸምህ ጊዜ፥ በአገርህ ደጅ ውስጥ ይበሉ ዘንድ ይጠግቡም ዘንድ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም ስጣቸው። |
| 13. | በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል። የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ወስጄ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም እንዳዘዝኸኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፥ አልረሳሁምም፤ |
| 14. | በኀዘኔ ጊዜ እኔ ከእርሱ አልበላሁም፥ ለርኵስነቴም ከእርሱ አላወጣሁም፥ ከእርሱም አንዳች ለሞተ ሰው አልሰጠሁም፤ የአምላኬንም የእግዚአሔርን ቃል ሰምቼአለሁ፥ ያዘዝኸኝንም ሁሉ አድርጌአለሁ። |
| 15. | ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደ ማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈስሰውን አገር ባርክ። |
| 16. | አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። |
| 17. | አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል። |
| 18. | እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ |
| 19. | ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል። |
| ← Deuteronomy (26/34) → |