Deuteronomy (21/34)  

1. አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር የተገደለ ሰው በሜዳ ወድቆ ቢገኝ፥
2. ገዳዩም ባይታወቅ፥ ሽማግሌዎችህና ፈራጆችህ ወጥተው በተገደለው ሰው ዙሪያ እስካሉት ከተሞች ድረስ በስፍር ይለኩ፤
3. ወደ ተገደለውም ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችውን ቀንበርም ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፤
4. የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ጊደሪቱን ይዘው ፈሳሽ ውኃ ወዳለበት ወዳልታረሰና ዘርም ወዳልተዘራበት ሸለቆ ይሄዳሉ፤ በዚያም በሸለቆው ውስጥ የጊደሪቱን አንገት ይሰብራሉ።
5. የሌዊ ልጆች ካህናትም ይቀርባሉ፤ በፊቱ እንዲያገለግሉ፥ በስሙም እንዲባርኩ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦአቸዋልና፥ በእነርሱም ቃል ክርክር ሁሉ ጉዳትም ሁሉ ይቈረጣልና፤
6. ወደ ተገደለው ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ አንገትዋ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ሲታጠቡ።
7. እጃችን ይህን ደም አላፈሰሰችም፥ ዓይናችንም አላየችም፤
8. አቤቱ፥ የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቍጠር ብለው ይናገራሉ። ስለ ደሙም ይሰረይላቸዋል።
9. አንተም በእግዚአብሔር ዓይን የቀናውን ባደረግህ ጊዜ የንጹሑን ደም በደል ከመካከልህ ታርቃለህ።
10. ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በማረክሃቸውም ጊዜ፥
11. በተማረኩት መካከል የተዋበች ሴት ብታይ፥ ብትመኛትም ሚስትም ልታደርጋት ብትወድድ፥ ወደ ቤትህ ታመጣታለህ፤
12. እርስዋም ራስዋን ትላጫለች፥ ጥፍርዋንም ትቈረጣለች፤
13. የተማረከችበትንም ልብስ ታወልቃለች፥ በቤትህም ተቀምጣ ስለ አባትዋና ስለ እናትዋ አንድ ወር ሙሉ ታለቅሳለች፤ ከዚያም በኋላ ትደርስባታለህ፥ ባልም ትሆናታለህ፥ እርስዋም ሚስት ትሆንልሃለች።
14. ከዚያም በኋላ በእርስዋ ደስ ባይልህ አርነት አውጥተህ ወደ ወደደችው ትሰድዳታለህ፤ በዋጋ ግን አትሸጣትም፤ እፍረት አድርገህባታልና እንደ ባሪያ አትቈጥራትም።
15. ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኵሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥
16. ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኵሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኵር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤
17. ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኵር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኃይሉ መጀመሪያ ነውና በኵርነቱ የእርሱ ነው።
18. ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥
19. አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖሩበትም ስፍራ በር ያምጡት፤
20. የከተማውንም ሽማግሌዎች። ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፥ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው።
21. የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ።
22. ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥
23. በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።

  Deuteronomy (21/34)