| ← Deuteronomy (20/34) → |
| 1. | ጠላቶችህን ለመውጋት በወጣህ ጊዜ፥ ፈረሶችንና ሰረገሎችን ሕዝቡንም ከአንተ ይልቅ በዝተው ባየህ ጊዜ፥ ከግብፅ አገር ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና አትፍራቸው። |
| 2. | ወደ ሰልፍም በቀረባችሁ ጊዜ ካህኑ ይቅረብ ለሕዝቡም እንዲህ ብሎ ይንገራቸው። |
| 3. | እስራኤል ሆይ፥ ስሙ፤ ዛሬ ጠላቶቻችሁን ለመውጋት ትቀርባላችሁ፤ ልባችሁ አይታወክ፥ አትፍሩ፥ አትንቀጥቀጡ፥ በፊታቸውም አትደንግጡ፤ |
| 4. | ከእናንተ ጋር የሚሄድ፥ ያድናችሁም ዘንድ ጠላቶቻችሁን ስለ እናንተ የሚወጋ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና። |
| 5. | አለቆችም ለሕዝቡ እንዲህ ብለው ይናገሩ። አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያስመርቀው ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። |
| 6. | ወይንም ተክሎ ፍሬውንም ያልበላ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው ፍሬውን እንዳይበላ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። |
| 7. | ሚስትም አጭቶ ያላገባትም ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያገባት ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። |
| 8. | አለቆቹም ደግሞ ጨምረው። ማንም ፈሪና ድንጉጥ ሰው ቢሆን እርሱ ፈርቶ የወንድሞቹን ልብ ደግሞ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ ብለው ለሕዝቡ ይናገሩ። |
| 9. | አለቆቹም ለሕዝቡ ነግረው በጨረሱ ጊዜ በየጭፍራው በሕዝቡ ላይ የጦር አለቆችን ይሹሙ። |
| 10. | ለመዋጋት ወደ አንዲት ከተማ በደረስህ ጊዜ አስቀድመህ በዕርቅ ቃል ጥራቸው። |
| 11. | የዕርቅ ቃልም ቢመልሱልህ ደጅም ቢከፍቱልህ፥ በከተማ ውስጥ ያለው ሕዝብ ሁሉ ይገብሩልህ ያገልግሉህም። |
| 12. | የዕርቅ ቃልም ባይመልሱልህ ከአንተም ጋር መዋጋት ቢወድዱ፥ አንተ ከተማይቱን ትከብባለህ ታስጨንቃትማለህ፤ |
| 13. | አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣት ጊዜ፥ በእርስዋ ያሉትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ስለት ትገድላቸዋለህ፤ |
| 14. | ነገር ግን ሴቶቹንና ሕፃናትን እንስሶቹንም በከተማይቱም ያለውን ምርኮ ሁሉ በዝብዘህ ለአንተ ትወስዳለህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የጠላቶችህን ምርኮ ትበላለህ። |
| 15. | የእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ባይደሉት ከአንተ እጅግ በራቁት ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ታደርጋለህ። |
| 16. | ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ከሚሰጥህ ከእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ምንም ነፍስ አታድንም። |
| 18. | ነገር ግን ለአማልክቶቻቸው ያደረጉትን ርኵሰት ሁሉ ታደርጉ ዘንድ እንዳያስተምሩአችሁ፥ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት እንዳትሠሩ፥ አምላክህ እግዚአብሔር እንዳዘዘህ ኬጢያዊውን አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽመህ ታጠፋቸዋለህ። |
| 19. | ከተማይቱን ለመውሰድ በመውጋት ብዙ ቀን ከብበህ ባስጨነቅሃት ጊዜ፥ ምሳርህን አንሥተህ ዛፎችዋን አትቍረጥ፤ ከእነርሱ ትበላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋው የምድር ዛፍ ሰው መሆኑ ነውን? |
| 20. | ለመብል የማይሆኑትን የምታውቃቸውን ዛፎች ታጠፋቸዋለህ፥ ትቈርጣቸውማለህ፤ እስክታሸንፋትም ድረስ በምትዋጋህ ከተማ ላይ ምሽግ ትመሽጋለህ። |
| ← Deuteronomy (20/34) → |