Deuteronomy (14/34)  

2. እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና ስለ ሞተው ሰው አካላችሁን አትንጩ፥ በዓይኖቻችሁም መካከል ራሳችሁን አትላጩ።
4. ርኩስን ነገር ሁሉ አትብላ። የምትበሉአቸው እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ በሬ፥
5. በግ፥ ፍየል፥ ዋላ፥ ሚዳቋ፥ የበረሃ ፍየል፥ አጋዘን፥ አጭ፥ በራይሌ፥ ድኵላ።
6. ከእንስሶች ሰኮናው የተሰነጠቀውን፥ ጥፍሩም ከሁለት የተከፈለውን፥ የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ።
7. ነገር ግን ከሚያመሰኩ ወይም ሰኮናቸው ከተሰነጠቀ እነዚህን አትበሉም፤ ግመልን፥ ጥንቸልን፥ ሽኮኮን አትበሉም። ያመሰኳሉና፥ ነገር ግን ሰኮናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሶች ናቸው።
8. እርያም፥ ሰኮናው ስለ ተሰነጠቀ ነገር ግን ስላላመሰኳ እርሱ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ ሥጋውን አትብሉ፥ በድኑንም አትንኩ።
9. በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፤ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ።
10. ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸውን አትበሉም፤ ለእናንተ ርኩስ ናቸው።
11. ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ።
12. ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፤
13. ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭልፊት፥ ጭላት በየወገኑ፥
15. ቍራም ሁሉ በየወገኑ፥ ሰጎን፥
16. ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥ ጕጕት፥
17. ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥
18. እርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።
19. የሚበርርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ አይበላም።
20. ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ።
21. አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነህና የበከተውን ሁሉ አትብላ፤ ይበላው ዘንድ በአገርህ ደጅ ለተቀመጠ መጻተኛ ትሰጠዋለህ፥ ወይም ለእንግዳ ትሸጠዋለህ። የፍየሉን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል።
22. ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ።
23. ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ።
24. አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ ትሸጠዋለህ፥
25. የዋጋውንም ገንዘብ በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ።
26. በዚያም በገንዘቡ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ ወይም የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ ሰውነትህም የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፥ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል።
27. ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በአገርህ ደጅ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል።
28. በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን አሥራት ሁሉ አምጥተህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ታኖረዋለህ፤
29. ሌዋዊውም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በአገርህም ደጅ ያለ መጻተኛ ድሀ አደግም መበለትም መጥተው ይበላሉ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።

  Deuteronomy (14/34)