Amos (4/9)  

1. በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችጋረኞችንም የምታሰጨንቁ፥ ጌቶቻቸውንም። አምጡ እንጠጣ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ።
2. ጌታ እግዚአብሔር። እናንተን በሰልፍ ዕቃ፥ ቅሬታችሁንም በመቃጥን የሚወስዱበት ቀን፥ እነሆ፥ በላያችሁ ይመጣል ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል።
3. እያንዳንዳችሁ በየፊታችሁ በተነደለ ስፍራ ትወጣላችሁ፤ በሬማንም ትጣላላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4. የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላ ኑና ኃጢአትን አብዙ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን አሥራታችሁን አቅርቡ፤
5. እርሾ ካለበትም የምስጋናውን መሥዋዕት አቅርቡ፥ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6. በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥራት፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
7. መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፥ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ።
8. የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ወኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
9. በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፤ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በልቶአል፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
10. በግብጽ እንደ ነበረው ቸነፈርን ሰደድሁባችሁ፤ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፥ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ የሰፈራችሁንም ግማት ወደ አፍንጫችሁ አወጣሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
11. ሰዶምንና ገሞራን እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፥ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
12. ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ፥ እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ።
13. እነሆ፥ ተራሮችን የሠራ፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም አሳብ ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።

  Amos (4/9)