← Amos (3/9) → |
1. | የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ |
2. | እንዲህም ብሎአል። እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ። |
3. | በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን? |
4. | ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ ይጮኻልን? |
5. | ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን? |
6. | ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ክፉ ነገር በከተማ ላይ የመጣ እንደ ሆነ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን? |
7. | በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። |
8. | አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው? |
9. | በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና። በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ። |
10. | ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥ ይላል እግዚአብሔር። |
11. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድሪቱ ዙሪያ ጠላት ይመጣል፤ ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፥ አዳራሾችሽም ይበዘበዛሉ። |
12. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአልጋ ማዕዘን፥ በደማስቆም በምንጣፍ ላይ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ። |
13. | ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። |
14. | እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። |
15. | የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቆችም ቤቶች ይፈርሳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
← Amos (3/9) → |