Amos (1/9) → |
1. | በቴቁሔ ከላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ቃል ይህ ነው። |
2. | እንዲህም አለ። እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል። |
3. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። |
4. | በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። |
5. | የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር። |
6. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። |
7. | በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። |
8. | ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
9. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። |
10. | በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። |
11. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄንም ሁሉ ጥሎአልና፥ ቍጣውም ሁልጊዜ ቀድዶአልና፥ መዓቱንም ለዘላለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። |
12. | በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የባሶራንም አዳራሾች ትበላለች። |
13. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን እርጕዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። |
14. | በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በሰልፍም ቀን በጩኸት በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት አዳራሾችዋን ትበላለች፤ |
15. | ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር። |
Amos (1/9) → |