Acts (8/28)  

1. በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ።
2. በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።
3. ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር።
4. የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።
5. ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው።
6. ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ።
7. ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤
8. በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ።
9. ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ።
10. ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ። ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር።
11. ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር።
12. ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።
13. ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ።
14. በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው።
15. እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤
16. በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።
17. በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ።
18. ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና።
19. እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ።
20. ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው። የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።
21. ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም።
22. እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤
23. በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።
24. ሲሞንም መልሶ። ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው።
25. እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ።
26. የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው።
27. ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤
28. ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።
29. መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው።
30. ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው።
31. እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።
32. ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
33. በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?
34. ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው።
35. ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት።
36. በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።
37. ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።
38. ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።
39. ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።
40. ፊልጶስ ግን በአዛጦን ተገኘ፥ ወደ ቂሣርያም እስኪመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።

  Acts (8/28)