| ← Acts (19/28) → |
| 1. | አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ |
| 2. | አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም። አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። |
| 3. | እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም። በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። |
| 4. | ጳውሎስም። ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። |
| 5. | ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ |
| 6. | ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። |
| 7. | ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። |
| 8. | ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። |
| 9. | አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። |
| 10. | በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። |
| 11. | እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ |
| 12. | ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። |
| 13. | አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። |
| 14. | የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። |
| 15. | ክፉው መንፈስ ግን መልሶ። ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። |
| 16. | ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም። |
| 17. | ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ |
| 18. | አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። |
| 19. | ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። |
| 20. | እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር። |
| 21. | ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ። ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። |
| 22. | ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። |
| 23. | በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። |
| 24. | ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ |
| 25. | እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። |
| 26. | ይህም ጳውሎስ። በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል። |
| 27. | ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል። |
| 28. | ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ። |
| 29. | ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። |
| 30. | ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። |
| 31. | ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። |
| 32. | ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። |
| 33. | አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። |
| 34. | አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። |
| 35. | የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ። የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? |
| 36. | ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። |
| 37. | የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። |
| 38. | ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። |
| 39. | ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። |
| 40. | ዛሬ ስለ ተደረገው። ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና። |
| 41. | ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው። |
| ← Acts (19/28) → |