← Acts (12/28) → |
1. | በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። |
2. | የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። |
3. | አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ። |
4. | በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው። |
5. | ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። |
6. | ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። |
7. | እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። |
8. | መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ። |
9. | ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። |
10. | የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። |
11. | ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ። ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ። |
12. | ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። |
13. | ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ |
14. | የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። |
15. | እነርሱም። አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም። መልአኩ ነው አሉ። |
16. | ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። |
17. | ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና። ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። |
18. | በነጋም ጊዜ። ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን? ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። |
19. | ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ። |
20. | ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና። |
21. | በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤ |
22. | ሕዝቡም። የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ። |
23. | ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ። |
24. | የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር። |
25. | በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ። |
← Acts (12/28) → |