← Acts (11/28) → |
1. | ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። |
2. | ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው። |
3. | ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት። |
4. | ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ። |
5. | እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ |
6. | ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። |
7. | ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። |
8. | እኔም። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ። |
9. | ሁለተኛም። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። |
10. | ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። |
11. | እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። |
12. | መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። |
13. | እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና። ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ |
14. | እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል እንዳለው ነገረን። |
15. | ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው። |
16. | ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። |
17. | እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ? |
18. | ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና። እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ። |
19. | በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፥ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር። |
20. | ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ። |
21. | የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። |
22. | ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤ |
23. | እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤ |
24. | ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ። |
25. | በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤ |
26. | ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ። |
27. | በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ |
28. | ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ። |
29. | ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤ |
30. | እንዲህም ደግሞ አደረጉ፥ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት። |
← Acts (11/28) → |