2Samuel (9/24)  

1. ዳዊትም። ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው ቀርቶአልን? አለ።
2. ከሳኦልም ቤት ሲባ የሚባል አንድ ባሪያ ነበረ፥ ወደ ዳዊትም ጠሩት፤ ንጉሡም። አንተ ሲባ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ነኝ አለ።
3. ንጉሡም። የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው አልቀረምን? አለ። ሲባም ንጉሡን። እግሩ ሽባ የሆነ አንድ የዮናታን ልጅ አለ አለው።
4. ንጉሡም። ወዴት ነው? አለው፤ ሲባም ንጉሡን። እነሆ፥ እርሱ በሎዶባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት አለ አለው።
5. ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።
6. የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም። ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ ባሪያህ አለ።
7. ዳዊትም። ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው።
8. እርሱም። የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ የተመለከትህ እኔ ባሪያህ ምንድር ነኝ? ብሎ እጅ ነሣ።
9. ንጉሡም የሳኦልን ባሪያ ሲባን ጠርቶ። ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ።
10. አንተና ልጆችህ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፤ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግባ፤ የጌታህ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል አለው። ለሲባም አሥራ አምስት ልጆችና ሀያ ባሪያዎች ነበሩት።
11. ሲባም ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሡ ባሪያውን እንዳዘዘ እንዲሁ ባሪያህ ያደርጋል አለው። ሜምፊቦስቴም ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ገበታ ይበላ ነበር።
12. ለሜምፊቦስቴም ሚካ የተባለ ታናሽ ልጅ ነበረው። በሲባም ቤት ያሉ ሁሉ ለሜምፊቦስቴ ያገለግሉ ነበር።
13. ሜምፊቦስቴም ከንጉሥ ገበታ ሁልጊዜ እየበላ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት እግሩም ሽባ ነበረ።

  2Samuel (9/24)