| ← 2Samuel (5/24) → |
| 1. | የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን። |
| 2. | አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም። አንተ ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ ትሆናለህ ብሎህ ነበር አሉት። |
| 3. | የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሡ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በእስራኤልም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት። |
| 4. | ዳዊትም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ልጅ ነበረ፥ አርባ ዓመትም ነገሠ። |
| 5. | በኬብሮን በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። |
| 6. | ንጉሡና ሰዎቹም በአገሩ ውስጥ ከተቀመጡት ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም። ዳዊት ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበርና ዳዊትን። ዕውሮችንና አንካሶችን ካላወጣህ በቀር ወደዚህ አትገባም አሉት። |
| 7. | ነገር ግን ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፥ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት። |
| 8. | በዚያም ቀን ዳዊት። ኢያቡሳውያንን የሚመታ በውኃ መሄጃው ይውጣ፤ የዳዊትም ነፍስ የምትጠላቸውን ዕውሮችንና አንካሶችን ያውጣ አለ። ስለዚህም በምሳሌ። ዕውርና አንካሳ ወደ ቤት አይግቡ ተባለ። |
| 9. | ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፥ የዳዊትም ከተማ ብሎ ጠራት። ዳዊትም ዙሪያዋን ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ ቀጠራት። |
| 10. | ዳዊትም እየበረታ ሄደ፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። |
| 11. | የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም አናጢዎችንም ጠራቢዎችንም ላከ፤ ለዳዊትም ቤት ሠሩለት። |
| 12. | ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው፥ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ። |
| 13. | ዳዊትም ከኬብሮን ከመጣ በኋላ ሌሎቹን ቁባቶቹንና ሚስቶቹን ከኢየሩሳሌም ወሰደ፤ ለዳዊትም ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። |
| 14. | በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት ስማቸው ይህ ነው፤ ሳሙስ፥ |
| 15. | ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ |
| 16. | ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት። |
| 17. | ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ምሽጉ ወረደ። |
| 18. | ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። |
| 19. | ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን። ፍልስጥኤማውያንን በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው። |
| 20. | ዳዊትም ወደ በኣልፐራሲም መጣ፥ በዚያም መታቸውና። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በፊቴ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣልፐራሲም ብሎ ጠራው። |
| 21. | ጣዖቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው። |
| 22. | ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ መጡ፥ በራፋይምም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። |
| 23. | ዳዊትም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ አትውጣ። |
| 24. | በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ፥ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያን ጊዜ ቸኵል አለው። |
| 25. | ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ። |
| ← 2Samuel (5/24) → |