| ← 2Samuel (4/24) → | 
| 1. | የሳኦልም ልጅ ኢያቡስቴ አበኔር በኬብሮን እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ እጁ ደከመች፥ እስራኤላውያንም ሁሉ ደነገጡ። | 
| 2. | ለሳኦልም ልጅ ለኢያቡስቴ የጭፍራ አለቆች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንዱም ስም በዓና፥ የሁለተኛውም ስም ሬካብ ነበረ፥ ከብንያምም ልጆች የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮትም ለብንያም ተቈጥራ ነበር። | 
| 3. | ብኤሮታውያንም ወደ ጌቴም ሸሽተው ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ተጠግተው ነበር። | 
| 4. | ለሳኦልም ልጅ ለዮናታን አንድ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። የሳኦልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ፥ ሞግዚቱም አዝላው ሸሸች፤ ፈጥናም ስትሸሽ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜምፊቦስቴ ነበር። | 
| 5. | የብኤሮታዊውም የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ቀኑ ሲሞቅ ወደ ኢያቡስቴ ቤት መጡ፤ እርሱም በቀትር ጊዜ በምንጣፍ ላይ ተኝቶ ነበር። | 
| 6. | በረኛይቱም ስንዴ ታበጥር ነበር፥ አንቀላፍታም ተኝታ ነበር፤ ሬካብና ወንድሙ በዓናም በቀስታ ገቡ። | 
| 7. | ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ እርሱ በእልፍኙ በምንጣፉ ላይ ተኝቶ ሳለ መቱት፥ ገደሉትም፤ ራሱንም ቈርጠው ወሰዱት፥ በዓረባም መንገድ ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ። | 
| 8. | የኢያቡስቴንም ራስ ይዘው ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጡ፥ ንጉሡንም። ነፍስህን ይሻ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ እነሆ፤ እግዚአብሔርም ዛሬ ከሳኦልና ከዘሩ ለጌታችን ለንጉሥ ተበቀለለት አሉት። | 
| 9. | ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞት ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነ ሕያው እግዚአብሔርን! | 
| 10. | መልካም ወሬ የያዘ መስሎት። እነሆ፥ ሳኦል ሞተ ብሎ የነገረኝን የምስራቹ ዋጋ እንዲሆን ይዤ በጺቅላግ ገደልሁት። | 
| 11. | ይልቁንስ በቤቱ ውስጥ በምንጣፉ ላይ ንጹሑን ሰው የገደላችሁትን እናንተን ኃጢአተኞችንማ እንዴት ነዋ? ደሙን ከእጃችሁ አልሻውምን? ከምድርም አላጠፋችሁምን? | 
| 12. | ዳዊትም ጕልማሶቹን አዘዘ፥ ገደሉአቸውም፤ እጃቸውንና እግራቸውን ቈርጠው በኬብሮን በውኃ መቆሚያ አጠገብ አንጠለጠሉአቸው። የኢያቡስቴንም ራስ ወስደው በአበኔር መቃብር በኬብሮን ቀበሩት። | 
| ← 2Samuel (4/24) → |