| ← 2Samuel (23/24) → |
| 1. | የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤ |
| 2. | የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ። |
| 3. | የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ። በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥ |
| 4. | እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል። |
| 5. | በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ አይደለምን? ከእኔም ጋር በሁሉ ነገር ቅንና ጽኑ የሆነውን የዘላለም ቃል ኪዳን አድርጎአል፤ መድኃኒቴንና ፈቃዴን ሁሉ ያበቅላል። |
| 6. | ዓመፀኞች ሁሉ ግን ሰው በእጁ እንደማይዘው፥ እንደ ተጣለ እሾህ ናቸው። |
| 7. | ማናቸውም ሰው ይነካው ዘንድ ቢወደድ፥ በእጁ ብረትና የጦሩን የቦ ይይዛል፤ በሥራቸውም በእሳት ፈጽሞ ይቃጠላሉ። |
| 8. | የዳዊት ኃያላን ስም ይህ ነው። የአለቆች አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ያህል በአንድ ጊዜ ገደለ። |
| 9. | ከእርሱም በኋላ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከሦስቱ ኃያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ። |
| 10. | እርሱ ግን ተነሥቶ እጁ እስኪደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። |
| 11. | ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት እርሻ በአንድነት ሆነው ተከማችተው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። |
| 12. | እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኃኒትአደረገ። |
| 13. | ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። |
| 14. | በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። |
| 15. | ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ። |
| 16. | ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ። |
| 17. | አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። |
| 18. | የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሠላሳው አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ተጠርቶ ነበር። |
| 19. | እርሱ በሠላሳው መካከል የከበረ አልነበረምን? ስለዚህ አለቃቸው ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። |
| 20. | በቀብጽኤል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የቀብስኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። |
| 21. | ረጅሙንም ግብጻዊ ሰው ገደለ፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው። |
| 22. | የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። |
| 23. | ከሠላሳውም ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በክብር ዘበኞቹ ላይ ሾመው። |
| 24. | የኢዮአብም ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፥ የቤተ ልሔም ሰው የዱዲ |
| 25. | ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ ሒሮዳዊው ኤሊቃ፥ |
| 26. | ፈልጣዊው ሴሌስ፥ የቴቁሐዊው |
| 27. | የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው |
| 28. | አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ምቡናይ፥ አሆሃዊው |
| 29. | ጸልሞን፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን |
| 30. | ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው |
| 31. | ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ በርሑማዊው |
| 32. | ዓዝሞት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ |
| 33. | የአሳን ልጆች፥ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሣማ |
| 34. | የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የማዕካታዊው ልጅ የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥ |
| 35. | ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ አርባዊው ፈዓራይ፥ |
| 36. | የሱባ ሰው የናታን ልጅ ይግዓል፥ ጋዳዊው |
| 37. | ባኒ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሞናዊው ጼሌቅ፥ ብኤሮታዊው |
| 38. | ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው |
| 39. | ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፤ ሁሉ በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው። |
| ← 2Samuel (23/24) → |