← 2Samuel (18/24) → |
1. | ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው። |
2. | ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሲሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን። እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው። |
3. | ሕዝቡ ግን። አትወጣም፤ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፤ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፤ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአስሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፤ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ። |
4. | ንጉሡም። መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ። |
5. | ንጉሡም እዮአብንና አቢሳን ኢታይንም። ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለአቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ። |
6. | ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ሰልፉም በኤፍሬም ሁሉ ውስጥ ሆነ። |
7. | በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሃያ ሺህ ሰውም ሞተ። |
8. | ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፤ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ። |
9. | አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፤ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ። |
10. | አንድ ሰውም አይቶ። እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው። |
11. | ኢዮአብም ለነገረው ሰው። እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አስር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው። |
12. | ሰውዮውም ኢዮአብን። እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም። ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር። |
13. | እኔ ቅሉ በነብሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሳህብኝ ነበር አለው። |
14. | ኢዮአብም። እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው። |
15. | አስሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት። |
16. | ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ። |
17. | አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ። |
18. | አቤሴሎምም ሕያው ሳለ። ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሃውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሃውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል። |
19. | የሳዶቅ ልጅ አኪማኣስ ግን። እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ። |
20. | ኢዮአብም። በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፤ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው። |
21. | ኢዮአብም ኵሲን። ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነስቶ ሮጠ። |
22. | ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን። የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም። ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ። |
23. | እርሱም። እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም። ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንደር በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው። |
24. | ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ወጣ፥ ዓይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ። |
25. | ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም። ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ። |
26. | እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ። እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም። እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ። |
27. | ዘበኛውም። የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፤ ንጉሡም። እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካምም ወሬ ያመጣል አለ። |
28. | አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን። ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፍቶ። በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሱትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ። |
29. | ንጉሡም። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም። ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት። |
30. | ንጉሡም። ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፤ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ። |
31. | እነሆም፥ ኵሲ መጣ፤ ኵሲም። እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቻለሁ አለ። |
32. | ንጉሡም ኵሲን። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለው። ኵሲም። የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት። |
33. | ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር። ች |
← 2Samuel (18/24) → |