← 2Samuel (10/24) → |
1. | ከዚህ በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ሞተ፥ ልጁም ሐኖን በፋንታው ነገሠ። |
2. | ዳዊትም። አባቱ ወረታ እንዳደረገልኝ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው ባሪያዎቹን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ አሞን ልጆች አገር መጡ። |
3. | የአሞንም ልጆች አለቆች ጌታቸውን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ ሊያጽናናህ ባሪያዎቹን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ዳዊትስ ከተማይቱን ለመመርመርና ለመሰለል ለማጥፋትም ባሪያዎቹን የላከ አይደለምን? አሉት። |
4. | ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ የጢማቸውን ገሚስ ላጨ፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። |
5. | ዳዊትም ያን በሰማ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበሩና ተቀባዮች ላከ። ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አላቸው። |
6. | የአሞን ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደተጠሉ ባዩ ጊዜ፥ የአሞን ልጆች ልከው ከሶርያውያን ከቤትሮዖብና ከሱባ ሀያ ሺህ እግረኞች፥ ከመዓካ ንጉሥም አንድ ሺህ ሰዎች፥ ከጦብም አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ። |
7. | ዳዊትም በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። |
8. | የአሞንም ልጆች ወጥተው በበሩ መግቢያ ፊት ለፊት ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን፥ የጦብና የመዓካም ሰዎች ለብቻቸው በሰፊ ሜዳ ላይ ነበሩ። |
9. | ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦቹን ሁሉ መረጠ፥ በሶርያውያንም ፊት ለሰልፍ አኖራቸው። |
10. | የቀረውንም ሕዝብ በወንድሙ በአቢሳ እጅ አድርጎ በአሞን ልጆች ፊት ለሰልፍ አኖራቸው። |
11. | ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ፤ የአሞን ልጆች ቢበረቱብህ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ። |
12. | አይዞህ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ። |
13. | ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። |
14. | የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ፤ ኢዮአብም ከአሞን ልጆች ዘንድ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። |
15. | ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ በአንድነት ተሰበሰቡ። |
16. | አድርአዛርም ልኮ በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን፥ አመጣ፤ ወደ ኤላምም መጡ፥ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶባክ በፊታቸው ነበረ። |
17. | ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ ወደኤላም መጣ፤ ሶርያውያንም በዳዊት ፊት ተሰልፈው ከእርሱ ጋር ተዋጉ። |
18. | ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ። |
19. | ለአድርአዛርም የሚገብሩ ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ታረቁ፥ ገበሩላቸውም። ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ ፈሩ። |
← 2Samuel (10/24) → |