| 2Samuel (1/24) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ። |
| 2. | በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ። |
| 3. | ዳዊትም። ከወዴት መጣህ? አለው እርሱም። ከእስራኤል ሰፈር ኰብልዬ መጣሁ አለው። |
| 4. | ዳዊትም። ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ። ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ። |
| 5. | ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው። |
| 6. | ወሬኛውም ጕልማሳ አለ። በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኵዞ ቆሞ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። |
| 7. | ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁ። |
| 8. | እርሱም። አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም። አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። |
| 9. | እርሱም። ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። |
| 10. | እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት። |
| 11. | ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ። |
| 12. | በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። |
| 13. | ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። አንተ ከወዴት ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት። |
| 14. | ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው። |
| 15. | ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ። ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም። |
| 16. | ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው። |
| 17. | ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኀዘን ቅኔ ተቀኘ፥ |
| 18. | የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል። |
| 19. | የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ! |
| 20. | የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቈላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ። |
| 21. | እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ። |
| 22. | ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም። |
| 23. | ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። |
| 24. | የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት። |
| 25. | ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል። |
| 26. | ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ። |
| 27. | ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ! |
| 2Samuel (1/24) → |