2Kings (7/25)  

1. ኤልሳዕም። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ።
2. ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ። ፕ
3. በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም። እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን?
4. ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፥ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን ተባባሉ።
5. ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም።
6. እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም። እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል ይባባሉ ነበር።
7. ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ።
8. እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ ጠጡም፥ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፥ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።
9. ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው። መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፥ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተ ሰብ እንናገር ተባባሉ።
10. መጥተውም። ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፥ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፥ የሰውም ድምፅ አልነበረም ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ።
11. የደጁም ጠባቂዎች ጠሩ፥ ለንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ።
12. ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን። ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ። ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፥ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል አላቸው።
13. ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ። በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፥ እንይም አለ።
14. ሁለትም ሰረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም። ሄዳችሁ እዩ ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ።
15. በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት።
16. ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ።
17. ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ።
18. የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ።
19. ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? ብሎ ነበር፤ እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም ብሎት ነበር።
20. እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።

  2Kings (7/25)