2Kings (4/25)  

1. ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት። ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።
2. ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም። ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች።
3. እርሱም። ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም አላት።
4. ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ።
5. እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር።
6. ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን። ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም። ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ።
7. መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም። ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ።
8. አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።
9. ለባልዋም። ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።
10. ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው።
11. አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ።
12. ሎሌውንም ግያዝን። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው።
13. በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም። እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት አለው፤ እርስዋም። እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች።
14. እርሱም። እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም። ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ።
15. እርሱም። ጥራት አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች።
16. እርሱም። በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ፤ እርስዋም። አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች።
17. ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።
18. ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ።
19. አባቱንም። ራሴን ራሴን አለው፤ እርሱም ሎሌውን። ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው አለው።
20. አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም።
21. ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች።
22. ባልዋንም ጠርታ። ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ አለችው።
23. እርሱም። መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
24. አህያውንም አስጭና ሎሌዋን። ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ አለችው።
25. እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤
26. ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና። በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት አለው። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
27. ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ።
28. እርስዋም። በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን? አለች።
29. ግያዝንም። ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር አለው።
30. የሕፃኑም እናት። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት።
31. ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ። ሕፃኑ አልነቃም ብሎ ነገረው።
32. ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።
33. ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
34. መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።
35. ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።
36. ግያዝንም ጠርቶ። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ። ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ አላት።
37. ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።
38. ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም። ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው።
39. አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም።
40. ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ፤ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም።
41. እርሱም። ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።
42. አንድ ሰውም ከበኣልሻሊሻ የበኵራቱን እንጀራ፥ ሀያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ እርሱም። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
43. ሎሌውም። ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው እሰጣለሁ? አለ። እርሱም። ይበላሉ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
44. እንዲሁም በፊታቸው አኖረው፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፥ አተረፉም።

  2Kings (4/25)