2Kings (22/25)  

1. ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች።
2. በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ቀኝም ግራም አላለም።
3. በንጉሡም በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፥ እንዲህም አለው።
4. የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ።
5. በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥
6. ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይም ወቃሪዎች፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት።
7. ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ነበሩና በእጃቸው ስለ ተሰጠ አይቈጣጠሩአቸውም ነበር።
8. ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን፥ የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፥ እርሱም አነበበው።
9. ጸሐፊውም ሳፋን ወደ ንጉሡ መጣ፥ ለንጉሡም። በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት፥ በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት ብሎ አወራለት።
10. ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው።
11. ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
12. ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን።
13. አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው።
14. እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ።
15. እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ።
17. በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።
18. እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥
19. እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።
20. ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።

  2Kings (22/25)