2Kings (21/25)  

1. ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱ ስም ሐፍሴባ ነበረ።
2. እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3. አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበኣል መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም።
4. እግዚአብሔርም። ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ።
5. በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።
6. ልጁንም በእሳት አሳለፈ፥ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7. እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤
8. ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ።
9. ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።
10. እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት እጅ እንዲህ ሲል ተናገረ።
11. የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ርኵሰት አድርጎአልና፥ ከፊቱም የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና
12. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።
13. የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።
14. የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፥ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤
15. አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና።
16. ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኃጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።
17. የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኃጢአት፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
18. ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
19. አሞጽም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሜሶላም ነበረች።
20. አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ።
21. አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ ሰገደላቸውም።
22. የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።
23. የአሞጽም ባሪያዎች አሴሩበት ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት፥
24. የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት።
25. የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
26. በዖዛም አትክልት ባለው በመቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

  2Kings (21/25)