2Kings (20/25)  

1. በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው።
2. ፊቱንም ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
3. አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።
4. ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት።
5. ተመልሰህ የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ።
6. በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።
7. ኢሳይስም፥ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ አለ፤ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደርጉለት፥ እርሱም ተፈወሰ።
8. ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድር ነው? አለው።
9. ኢሳይያስም፥ እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ወይም አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ ዘንድ ትወድዳለህን? አለ።
10. ሕዝቅያስም፥ ጥላው አሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ አለው።
11. ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውንም በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት ላይ በወረደበት መንገድ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መለሰው።
12. በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ።
13. ሕዝቅያስም ደስ አለው፥ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም።
14. ነቢዩም ኢሳያሳ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ። እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ? አለው። ሕዝቅያስም። ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ አለው።
15. እርሱም። በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም። በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው።
16. ኢሳይያስም ሕዝቅያስን። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።
17. እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር።
18. ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ አለው።
19. ሕዝቅያስም ኢሳይያስን። የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም። በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን? አለ።
20. የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውንም እንደ ሠራ፥ ውኃውንም ወደ ከተማይቱ እንዳመጣ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21. ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

  2Kings (20/25)