2Kings (2/25)  

1. እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።
2. ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።
3. በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው።
4. ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ።
5. ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ።
6. ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ።
7. ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።
8. ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።
9. ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
10. እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።
11. ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
12. ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።
13. ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።
14. ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።
15. ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።
16. እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው።
17. እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።
18. በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው። v
19. የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት።
20. እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት።
21. ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ።
22. ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።
23. ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት።
24. ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።
25. ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

  2Kings (2/25)