| ← 2Kings (15/25) → |
| 1. | በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ። |
| 2. | መንገሥም በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። |
| 3. | አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። |
| 4. | ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። |
| 5. | እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፥ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ፥ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፥ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሥ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለአገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር። |
| 6. | የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
| 7. | ዓዛርያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| 8. | በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ። |
| 9. | አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። |
| 10. | የኢያቤስም ልጅ ሰሎም ተማማለበት፥ በይብልዓም መትቶ ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። |
| 11. | የቀረውም የዘካርያ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። |
| 12. | ለኢዩ። ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ። |
| 13. | በይሁዳ ንጉሠ በዖዝያን በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ያህል ነገሠ። |
| 14. | የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ መጣ፥ በሰማርያም የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን መታ፥ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። |
| 15. | የቀረውም የሰሎም ነገር፥ የተማማለውም ዓመፅ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። |
| 16. | በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ቲፍሳን በእርስዋም ያሉትን ሁሉ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ቀደዳቸው። |
| 17. | በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ በሰማርያም አሥር ዓመት ነገሠ። |
| 18. | በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። |
| 19. | በዘመኑም የአሦር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ያጸናለት ዘንድ የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው። |
| 20. | ምናሔምም ብሩን ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለ ጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሦርም ንጉሥ ተመለሰ፥ በአገሪቱም አልተቀመጠም። |
| 21. | የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
| 22. | ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| 23. | በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ። |
| 24. | በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። |
| 25. | የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ተማማለበት፥ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር አምሳ የገለዓድ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፥ ፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። |
| 26. | የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። |
| 27. | በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሀያ ዓመትም ነገሠ። |
| 28. | በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። |
| 29. | በእስራኤልም ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮንና አቤልቤትመዓካን፥ ያኖዋንም፥ ቃዴስንና አሶርንም፥ ገለዓድንና ገሊላንም፥ የንፍታሌምን አገር ሁሉ ወሰደ፤ ወደ አሦርም አፈለሳቸው። |
| 30. | በዖዝያንም ልጅ በኢዮአታም በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ ተማማለ፥ መትቶም ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። |
| 31. | የቀረውም የፋቁሔ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። |
| 32. | በእስራኤል ንጉሥ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ። |
| 33. | መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ነበረች። |
| 34. | በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። |
| 35. | ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እርሱም የላይኛውን የእግዚአብሔርን ቤት በር ሠራ። |
| 36. | የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
| 37. | በዚያም ወራት እግዚአብሔር የሶርያን ንጉሥ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን በይሁዳ ላይ መስደድ ጀመረ። |
| 38. | ኢዮአታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| ← 2Kings (15/25) → |